Sunday, July 20, 2014

አንድ ለአምስት የወያኒቱ የስለላ ድር በዲያስፖራ



ይድረስ እንደ እኔ ከወገን ዘመዳችሁ ከሞቀ ቤታችሁና ከምትወዷት ሃገራችሁ ሳትወዱ በግድ እንጀራና ነጻነት ፈልጋችሁ ለተስደዳችሁ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ፡፡ በኔና እንደ እኔ ከሁለት ያጣ ሆነን ጭንቀቴንና እየደረሰብን ያለውን ከፍተኛ ችግር ለናንተ ላዋያችሁ በውስጤ እንደ ሰደድ እሳት የሚቆጠቁጠኝን ችግሬን ላካፍላችሁ ወገኖቼን አስቸግሬ ወደ እናንተ እንዲያስተላልፉልኝ ቆርጬ ስነሳ አብረውኝ


በነበሩ ሌሎች ወገኖቼም ሆነ በራሴ ጉዳት እንዳይደርስ በመጨነቅ የማወጋችሁ አሳዛኝ እህታችሁ ነኝ፡፡ እኔ ሳላውቅ የገባሁበት ችግር ውስጥ ሌሎችም ብዙ ወገኖቼ ክብደቱንና መዘዙን ስይገባቸው የሃገራችን ጠላት የወያኔይቱ ተላላኪዎች እየተጠቀሙባቸው ስለሆነ ላስጠነቅቃቸው ፈልጌና የራሴንም ሃጢያት እግረመንገዴን ለመናዘዝ ናው፡፡

ምርጫ 97ትን ተከትሎ በወገኖቼና በቅርብ ዘመዴ ላይ በደረሰው ግድያ ምክንያትና ተደናግጬና ተስፋ ቆርጬ ትምህርቴን አቅዋርጬ የተሻለ ህይወትም ጭምር ፍለጋ ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ወደ አረብ ሃገር ተሰደድኩኝ፡፡ ብዙዎቻችሁ እንደሰማችሁትና አንዶአንዶቻችሁም ደርሶባችሁ እንደምታውቁት ዘግናኝ የስቃይና የባርነት ህይወት ለአራት አመታት ተሰቃይቼ በፈጣሪ ፈቃድ ወደ አውሮፓ ጠፍቼ ስደርስ በህይወት እንድንኖር ፈጣሪ የፈቀደልን ብቻ ነበርነ ለጊዜውም ቢሆን ሰላም ሃገር የደረስነው፡፡   

በዚህ የፈተና ጉዞ ከረሃቡና የበረሃው ጉዞ ስቃይ በተጨማሪ በማንም የግመል እረኛና የስደተኛን ንብረት በመዝረፍ የጠገቡ አመላላሽ ነጋዴዎች ንብረታችንን ብቻ ሳይሆን የነበረንን የሰውነታችንን ክብርና እየተፈራረቁ በወንድሞቻችን ፊት ብዙ አሳፋሪ ለመናገር እንኳን የሚሰቀጥጥ ግፍ ተፈጽሞብናል፡፡ ወንድሞቻችንም እንደኛው የያዙትን ንብረትና ጥሪት ተገፈው እየተደበደቡ ደክመው ህይወታቸው ያለፈና በየበረሃው ካለቀባሪ አሸዋ በልቶ ያስቀራቸው ባህር ላይ ለአሳ ነባሪ የገበርናቸው ጥቂት አልነበሩም፡፡


ከዚህ ሁሉ ስቃይ ቦኋላ ፈጣሪ ይብቃሽ ብሎኝ የተጠለልኩበት የመጀመርያ የስደት ሃገር ወገኔ የወንዜ የሃገሬ ልጅ ነች ብዬ እውነተኛ ማንነቴንና አረብ ሃገር የት እሰራ እንደነበር ያጫወትኳት ተንኮለኛ ሚስጥሬን ካወቀች ቦኋላ ነበር ማንነቷን የተረዳሁት፡፡ ከብዙ መቀራረብ ቦኋላ ችግሬንና የውስጥ ሚስጥሬን ጠንቅቃ ከተረዳች ቦኋላ አዛኝ መስላ ለማንኝውም ወደ ሃገርሽ ቢመልሱሽ ችግር እንዳይገጥምሽ ወደ ተቃዋሚዎች እንዳትቀርቢ፡፡ እዚህ ከሚኖሩ የመንግስታችን ደጋፊዎች ጋር አብረሽ ከተደራጀሽ ምንም ክፉ ነገር ቢደርስብሽ ጥለው አይጥሉሽም ብላ ሳትጨርስ ነበር አንቀጥቅጦኝ ዘልዬ አንገቷን ያነኳት፡፡ 

ጸጉሯን ጨምድጄ ያ ሁሉ ያፈሰሳችሁት ደም ሳይደርቅ እዚህ ነጻ ሃገር ድረስ ተከተላችሁኝ ወይ? ብዬ እንዳበደ እየጮህኩኝ በጥርሴ ልዘለዝላት ስታገል ነበር የመጨረሻ የማስታውሰው፡፡ እብድ ናት ተብዬ እጅ እና እግሬ በካቴና ከአልጋዬ ጋር ተጠፍሮ ነበር የነቃሁት፡፡ ምን እንደወጉኝ ባላውቅም ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሚያፈዝ እንቅልፍ የሚያበዛና የሚጫጫን ነገር ጥሎብኝ አልፎዋል፡፡

ሲሻለኝ ስደት የጠየኩበት መስሪያ ቤት ዋስ ሆኖ መሰለኝ አስፈትቶኝ ወደ ነበርኩበት ካንፕ ሲመልሰኝ ይቺው ወያኔይቱ አሁንም ሳታፍር ቀርባኝ አረብ ሃገር ድረስ ተጻጽፋ እዛ በሚኖሩ ዘመዶችዋ አማካይነት አሰሪዎቼን ተገናኝታ ባልጠበኩት መንገድ የፓስፖርቴንና

የስራ ኮንትራት ፎቶ ኮፒ ቅጂ በእጇ እንዳለ አሳየችኝ፡፡ የጠየቀችኝን ባልተባበር ዶኪሜንቱን ለፖሊስና ለስደተኛ ክፍል እንደምታስረክብና ዲፕርት ተደርጌ ከቦሌ አየር ማረፊያ መንግስት ተቀብሎ ምን ሊደርስብኝ እንደሚችል ስትዘረዝርልኝ የታየችኝ እናቴ ዘንድ አደራ ያስቀመጥኳት ጨቅላ ልጄና ከሃገር መውጫ ቪዛ ተበድራና ንብረቷን አስይዛ የላከችኝ እናቴን ነበር ያስታወስኳት፡፡ እያለቀስኩኝ እህት አለም እንኳን የመንግስት ደጋፊ የፈለግሽውን አድርጊኝ እተባበርሻለሁ እባክሽ ኬዜን አታበላሺ ብዬ ነበር እግሯ ላይ የተንከባለልኩት፡፡                                                                                                   

ያበላሸሁትንና የነጨሁትን የአርቲፊሻል ጸጉር ከነመቀጫው አራት መቶ ዶላር ከፍዬ፡ አንድ ለአምስት በሚባል ትንሽ ማህበር እንድደራጅ እራስዋን ጨምሮ ሌሎች አራት ሰዎች እዛው አብረን የምንኖርና በፍጹም ጠርጥሬ የማላውቃቸው ሰዎች አስጠኗት ብላ አገናኘችኝ፡፡

አንዳንዶቹ እንደ እኔው ግራ የገባቸውና የማያምኑበትን ተገደው የተቀበሉ እንደሚያስመስሉ ብጠረርም እርስ በእርስ እንድንፈራራ እሷ በሌለችበት ያወራነውንና ያደረግነውን ለየብቻ ሄደው ስለሚነግሯትና ይህንንም እሷ እየመጣች እከሌ የደበቀኝን እከሊት ነገረችኝ እያለች እርስ በእርሳችን እያወጣጣች ስለምታጋጨን አንተማመንም፡፡ መንግስታችንን የሚቃወሙ ጸረ ሰላምና ጸረ እድገት የሆኑ የደርግ የኢሃፓ እና የቅንጅት ርዝራዦች ናቸው አትመኗቸው ካገኟችሁዋቸውም ምን እንደሚሉና ምን እየሰሩ እንደሆነ ለቡድናችን ሪፖርት አድርጉ ትለናለች፡፡ እንደ አጋጣሚ ሰው ካላገኘንና የምናስተላልፈው ሪፖርት ከሌለ በጸረ ልማቶች እንደተወናበድንና ሚስጥር መደበቅ እንደ ጀመርን ሌላ ሪፖርት እንደደረሳት ስለምታስፈራራን ከዚህ ሁሉ ስቃይ ለመውጣት ያልሆነ የሆነውን ወሬ እየነገርናት ከስቃይ ለመዳን እንሞክር ነበር፡፡ ይህ ህይወታችንን ለማትረፍ በወገኖቻችን ላይ ጀርባችንን አዙረን ህዝባችንን ከሚበድሉ ጎን መሰለፉ ውስጤን እየቆጠቆጠው ቢሆንም ነብሴ ስላሸነፈቺኝ ስተኛ ሁሌ አለቅሳለሁ፡፡ በውስጤበራሴ ላይ መተማመን ከመምከኑም በላይ የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን ሳይ መጥላ ጀመርኩኝ፡፡

ፈጣሪዬ ሊቀጣኝ መሰለኝ ይህንን ሁሉ ስህተት ተሳስቼም የተጠለልኩበት ሃገር ለመሰደድ የሰጠሁትን ምክንያት ስላልተቀበለኝ ወደ ሁለተኛውና አሁን ያለሁበት ሃገር በዚችው ሴትዮ በምታውቃቸው ሰዎች እርዳታ ገባሁ፡፡ የፈራሁት እውነት ሆኖ ተቀብለውኝ ያረፍኩበት ቤት፣ የስደት መጠየቂያውን መንገድ መንገዱን የሚመክሩኝና ኤርትራዊ ነኝ ብዬ እጄን እንድሰጥ ኬዝ የሚያስጠኑኝ እነዚሁ ከሃገር ያሰደደኝን መንግስት የሚደግፉ ጉዶች መሆናቸው ነገሩን ሁሉ ቅጥ አስጠፉብኝ፡፡ በተለይ ዋሽተው የሚረዱኝ ምክንያት ጸረ ልማቶችንና የድሮ ስራት ናፋቂዎችን እንደምቃወም በተላለፈልን መረጃ መስረት ነው እያሉ ያላሰብኩትና ያልጠበኩት ችግር ውስጥ ስለዶሉኝ ነገር ሁሉ

ተዘበራርቆብኝ ውሉ ጠፋብኝ፡፡ እንደማልደግፋቸውና እንደምቃወማቸው ልነግራቸው እየፈለኩኝ ነፍስና ስጋዬ ብቻ ሳይሆኑ የኔን እርዳታ የምትጠብቀው ህጻንና፣ ንብረቷን አስይዛ ለፓሳፖርቴና መጓጓዣ እዳ የገባችዋ እናቴ አሳዘኑኝ፡፡ ይህንን የምነግራችሁ እንድትራሩልኝና ጥፋቴን እንድታሳንሱት አይደለም፡፡

ክፉ ለሰራ ፈጣሪም ስለማይተባበረው ይሄ አዲስ የመጣሁበት ሃገር ኤርትራዊ መሆኔን ካለመቀበላቸውም ሌላ በጥያቄና መልስ ጊዜ ብዙ ነገር ስለተበላሸብኝ የስደት ጥያቄዬ ተሰርዞ ወደ ሃገራችሁ እንመልሳችኋለን ተብለን አንድ ካንፕ ውስጥ ወደ ሃገሬ እስክመለስ በጊዜያዊነት ያጉሩኛል፡፡ የተባለው ካንፕ ውስጥ ደርሼ ሱባኤ ገብቼ ለሰራሁት ሃጢያት እስከምመለስ እጸልያለሁ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ እንደደረስኩም ከማንም ላለመቀራረብ ወሰንኩኝ፡፡ በተለይ ማን ምን እንደሆነ መለየቱ ስለሚከብድ የሃገሬን ልጅ ሸሸሁ፡፡ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥመኝ መጠንቀቅና መደበቅ ጀመርኩኝ፡፡ ለሊትና ቀን አልጋዬ ላይ አሞኛል ብዬ ቤቴን ቆልፌ ማልቀስ ሆነ ስራዬ፡፡ ለጥቂት ቀናት ከሰው ብሸሽም እንደፈለኩትና እንደተመኘሁት አልሆነልኝም፡፡           

ባልጠበኩትና ባላሰብኩት መንገድ ስልክ ይፈልግሻል ተብዬ አንዲት አይቻት እንኳን ከማላውቃት ሴት በሬን ቆርቁራ የእጅ ሞባይሏን አቀበለችኝ፡፡ በማላውቀው ሰው ሞባይል ማን ይደውልልኛል ብዬ በመገረም ቀስ ብዬ ማዳመጥ ጀመርኩኝ፡፡ አዎ ያቺ መጀመርያ የቀረበችኝ ሃይለኛ ልጅ ከመጀመርያው የስደት ሃገር በስልክ ለወያኔዎቹ እንደ የገዛችው እቃ ልታረካክበኝ ነበር የደወለችው፡፡ የተቀበሉኝ ሰዎች የደረሰብኝን ሁኔታ ተከታትለው እስከ አዲሱ አድራሻዬ ነግረዋታል፡፡

የአዛኝ ቅቤ አንጓች ሁና ልታጽናናኝና አሁን ያለሁበት ካንፕ ከሚኖሩ ማህበርተኞቼ ልታገናኘኝ መሆኑ ነው፡፡ እዛ ካምፕ መምጣቴ እንደነገረቻቸውና እንደሚረዱኝ አስረዳችኝ፡፡ የነሱ አባል በመሆኔ ምክንያት ስሜ ለኤንባሲ እንደተላለፈና ሊያስወጡኝ ቢፈልጉ የመጓጓዣ ሰንድ ባለመስጠት እንደሚተባበሩኝ አብራራችልኝ፡፡ መንግስታችን አናውቃትም አንቀበላትም ብሎ ካልተባበረ የመኖርያ ፈቃድ በግድ እንደሚሰጡኝ ስትተነትንልኝ በፍርሃትና በድንጋጤ የሟሸሽኩትን እንደገና ነብስ ዘራችብኝ፡፡ ለካ ሳላውቀው የወያኔ ድርጅት አባል እንደሆንኩኝ ተነግሯቸው ኑሮ እንኳን ደህና መጣሽ ብለው ሁሉም ይስሙኝ ጀመር፡፡                                                                                                                                   

እሸሻቸዋለሁ ያልኩትን ረሳሁት፡፡ ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንዲሉ፡፡ አይዞሽ እኛም እንዳንቺ መጀመርያ ግራ ተጋብተን ነበር ቦኋላ ነው መንገድ መንገዱን እዚህ የቆዩ ሰዎች ያሳዩን፣ ነገ እዚህ ፈቃድ ያላትን ዋናዋን የማህበራችንን ሃላፊ እረዳታችንን መምጣትሽን ስለሰማች ቤትዋ ወስደን እናስተዋውቅሻለን አሉኝ፡፡ ሃገሬ ውስጥ ያለሁኝ ነበር ሁኖ የተሰማኝ፡፡ ከሃገር ሃገርና ከካንፕ ካንፕ ሲቀባበሉኝ ዓለሙን በሙሉ የገዙት ነበር የመሰለኝ፡፡ አረብ ሃገር ሁኜ አዳምጣቸው የነበሩ ያ ሁሉ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ተከታዮቻቸው ለካ በፓልቶክና በፌስ ቡክና በድህረ ገሳች ላይ ብቻ ናቸው እስከማለት ነበር የደረስኩት፡፡ 
ለመኖርያ ፈቃድ ብዬ የገባሁበት አንድ ለ አምስት ብሎ ነገር በተሃገሩና በመጠለያ ጣቢያው እንደ ጥላዬ እየተከተለኝና እንደ የሸረሪት ድር ዙርያችንን ላይ እየተጠመጠመ ነው፡፡ ህግና ስልጣኔ ያለበት ነጻ ሃገር አንዲት ትግሬኛ ተናጋሪ አስተባባሪያችን ይህንን ሁሉ የሰው ልጅ እንደ በግ እየነዳች እንደ ባርያ እያዘዘችን በጸረ ልማትና የድሮ መንግስት ናፋቂ ደርጎች ስም ስንቶቹ ወገኖቻችንን እየሰለልንና ስማቸውን እያበላሸን እንደነበር ሳስበው ይሰቀጥጠኛል፡፡

የተደላደለ ህይወት ያላት አለቃዪቱ ቤት ተሰብስበነ ስታስተናግደን አንዲትም ጊዜ ወያኔይቱን የማይደግፉትን ስደተኞች ተቃዋሚ የሚል ቃል ስትጠቀም አልሰማሁም፡፡ ያ ስም ወደ ጸረ ልማት ጸረ የአባይ ግድብ አሸባሪዎች የእስላም አክራሪዎች ተቀይሯል፡፡ በመጨረሻው የተጠለልኩበት ሃገር በሁለት የተለያየ የመጠለያ ካንፕ ቆይታዬ እንደ እኛ አንድ ለአምስት ተደራጅተው ወያኔይቱን ከሚደግፉ ሰዎቻቸው ጋር ተዋውቄያለሁ፡፡ በየቦታው ከላይ ሆነው የሚያዙን የሰሜኑ ወገኖቻችን ይሁኑ እንጂ ከአስር ዘጠኝ እጅ እንደ እኔ ከሌላ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ ጊዜው ከፍቶ በእንጀራው እየመጡበት ወገኑን መክዳትና አሳልፎ መስጠት የተለመደ ሆንዋል፡፡ የወያኔይቱ ስም በመንግስታት እንዳይወቀስ ኤርትራ ብላችሁ ስጡ የሚለው ተንኮል የገባኝ ኋላ ነው፡፡ የግለሰቡ ኬዝ ቢፈልግ ይበላሽ እንጂ አዲስ እጅ ያልሰጠ ሰው ሲመጣ የሚመከረው ኤርትራዊ ነኝ ብሎ እጅ እንዲሰጥ ነው፡፡                                                                                                                                                      

በእርግጥ በዛ መንገድ ፈቃድ ይቀላል ተብሎ ቢታመንም ዋናው ምክንያት ግን ወያኔይቱ በመንግስታት ወቅሳ እንዳይደርስባት ጭምር እንደሆነ ቦኋላ ከተቃዋሚዎች ሰምቻለሁ፡፡ ለነገሩ እንኳን ትግሬዎቹ እኛ በሙሉ ኤርትራዊ ሆነዋል፡፡ የእውነት ኤርትራውያኖቹም ግራ ገብታቸው ነው መሰል ከኛ ጋር አንድ ለአምስት መደራጀት ጀምረዋል፡፡ ለምን ያኔ እንዳስገነጠሏቸው እንጃ፡፡ ከኛው ጋር የመንግስት ተቃዋሚ የሚባሉትን ስም ያጠፋሉ፡፡ የሚሰሩትንና የሚናገሩትን ቀርቶ መሬት ላይ ጥብ ያለውን እየሰለሉ ሹክ ይላሉ፡፡ እነዚህ ብኩኖች ጓደኛ ዘመድ ትዳር ሚስት የማያውቁ ድንበር የለሽ ጉዶች ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ከእስፖርት ከህዝብ ስብሰባ ከተጋበዙበት ቤት ሲመለሱ እንዴት እንደነበር የተፈሳው አይቀራቸውም፡፡                         

ለመታመን ብለው አብረው የሚበሉ የሚጠጡትን ሁሉ ይሰልላሉ፡፡ አስላዮቹ እንኳን ይገምቱናል ብለው የማያፍሩ ለፍርፋሪ የተንበረከኩ ሃገር አሰዳቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ እኔንም አሳስተውኝ ነበር፡፡በተለይ እኛ ሴቶችን አለቃይቱ ከበላይ ምን ስትታዘዝ እንደሆን እንጃ ስልኪቷን በጠዋት ታቃጭልና አሁኑኑ አንቺና እከሊት አትራክቲቭ ሁናችሁ ስልክ ሳትደውሉ በቀጥታ እከሌ ቤት ሄዳችሁ በዚህ ስናልፍ ሰላም ልንልህ ነው ብላችሁ ግቡ፡፡ ስትደርሱ ምን ይሰራ እንደነበር አጥኑ፡፡ኮኒፒዩተር ላይ ከነበረም ምን ያነብ ወይም ይጽፍ እንደንበር አስተውሉ፡፡

የሆነ ነገር በኮንፒዩተር አሳየን ብላችሁ ሲከፍት የፓልቶክ ስሙን ለማየት ሞክሩ፡፡ ሻይ ቡና ሊላችሁ ወደ ኩሽና ሲገባ ጠረጴዛው ላይ ማስታወሻ ደብተር ወይም ብጣቂ ወረቀቶች ላይ የምታዩትን ስም አድራሻ ስልክ ቁጥር ለማስታወስ ወይም በጽሁፍ ለመያዝ ሞክሩ፡፡ ሌላም ጠቃሚ ነገር እንደ ዩአኤስቢ ካኛችሁ ውሰዱ፡፡ በሴትነታችሁ ተማርኮ የሚቀባዥረውን ከቻላችሁ በሞባይል ቅዱት፡፡ የማያስተውል ከሆነም ወደ መጸዳጃ ቤት ሄዳችሁ ምልክት ስጥታችሁኝ አሰሙኝ፡፡ ለፍቅር ለመቅረብ የሚፈልግ ከመሰላችሁ አደፋፍሯቸው

እንጂ እንዳይሸሽዋችሁ ፊት አትንሷቸው፡፡ ስትመለሱ ቡና እየጠጣን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እንጫወታለን፡፡ ለወደፊቱ መሻሻል የሚገባውንም እንዲሁ እንጫወታለን፡፡ይህንን ጸረ ልማትና ጸረ አባይ አቅዋማቸውን ካልቀየሩ አንድ ቀን በእጥፍ እናስከፍላቸዋለን ትለናለች፡፡ ኧረ ስንቱን ነግሬ ልጨርስላችሁ፡፡ ወሬ ካላመጣንላት ትግሉን እርግፍ አድርጋችሁ ትታችሁታል፡፡ እናንተ ተኝታችሁ

አሸባሪዎች እየተጠናከሩ ነው ለሃገራችሁ ስትታገሉ አትፍሩ፡፡ መንግስታችን ብዙ ወገኖቻችንን መስዋእት አድርገው ነው ከአንባ ገነን ወደ ልማታዊ መንግስት የመሰረቱልን፡፡ እናንተ ግን የምትረቡ አትመስሉም፡፡ ኤንባሲዎች እንዳትመለሱ ለሚተባበሯችሁ እንኳን ውለታ ለመመለስ የምትሳሱ አድር ባዮች ናችሁ፡፡ ኧረ ስንት አይነት የስድብ መአት ? እንዲያውም ትንሽ ወይን ቀማምሳ ያደረች ቀን ያስታውቅባታል እንደ የቀጠረችን ገረድ እንጂ እንደ ሰው አትቆጥረንም፡፡ የኛ የሴቶቹ ቀርቶ አሳማ ከነብሱ ውጠው የወፈሩ የሚመስሉ ወንዶች ከኛ ብሰው የአውራ ጣት ለምታክል ሴትዮ ወኔያቸው ፈሶ ወሬ በስልክ ወሬ ሲያመላልሱላት መስማቱ ያሳዝናል፡፡ እኔማ አንዳንዴ ምነው የአረብ ሃገር አሰሪዬን ጭነቅላቴን እየኮረኮመችና በጥፊ 
እያጠናገረችኝ የምትጮህብኝን አሰሪዬን እየመሰለችኝ መታነቅ የማስብባቸው ቀናት ብዙ ናቸው፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነን እኔም በስለላዬና የሰላማዊ ስደተኞችን ስም በማጥፋትና ደካማ ወንዶችንም በሴትነቴ ከጎልበቴ በላይ እየለብበስኩ ወያኔይቱንና እስዋ ካንፕ ውስጥ የሾመችልንን እያገለገልኩኝ ስልከሰከስ አንዲት የተባረከች ቀን ደረሰች፡፡ አለቂቱ በሞባይሌ ታቃጭልልኝና እንደተለመደው አሁኑኑ ያቺን ሴክሲ አለባበስሽን በደንብ አሳምረሽ በቅርብ ጠበቃሽ የላከልሽን ደብዳቤ ይዘሽ ነይ ትለኛለች፡፡ ወቅቱ በጣም የብርድ ጊዜ ስለነበር ሁሌ እንደማደርገው ከጉልበት በላይ መልበሱ ቀርቶ ብርዱ ተለብሶም አይቻልም፡፡ የሰውነቴን ቅርጽ በደንብ የሚያሳይ ልብስ ለብሼ ወፍራም ኮቴን ከላይ ደርቤና የእጅ ጋንቲዬን አጥልቄ በቅዝቃዜው እየተንቀጠቀጥኩኝ ቤቷ ደረስኩኝ፡፡ ሃገሩን እንደሚወድና ወያኔይቱን እንደሚቃወም ቀድሞም ልቤ ይጠረጥር የነበረና አሁን በትክክል የተረዳሁት ወገኔ ቤቱ ሄጄ የበሩን ደወል እንዳቃጭልና ከጠበቃዬ የተጻፈልኝን የማውቀውውን ደዳቤ እንዲተረጉምልኝ ለመግቢያ ምክንያት እንዳደርግ ትነግረኛለች፡፡ አንዴ እቤት ከገባሁ ቦኋላ ፍቅር ከመስራት በስተቀር በደንብ እያጫወትኩት እንዳዝናናው አስረድታኝ አንዳንድ ጥያቄ እንድጠይቀው ትንነግረኛለች፡፡ ተቃዋሚዎችን መተባበር ብፈልግ የቱ ነው ጥሩ? አላማቸው ምንድነው? ለስደተኛ ስንት መዋጮ

ታስከፍሉኛላችሁ? የሚለውን እየጠየኩኝ በስልክ እንድቀዳው በደንብ አሰናድታ ላከችኝ፡፡ ይህ ሰው ምን አቅዋም እንዳለውና የማን ተቃዋሚ አባል እንደሆነ ማወቅ የተቸገረች ብቻ ሳይሆን ፊት ስለሚነሳት ጠንዳ ይዛዋለች፡፡ እንደ ሌሎቹ ደካማ ወንዶች ለሴት ሲለሳለስ ሰዎች ስብስባ ስሙትማ ይህንን ተቃዋሚ ነኝ ባይ እያለች ስም ልታስቅበት ነው የተጣደፈችው፡፡ደጋግማ ስለ ትቢቱ ስታወራ ስለሰማሁ በኔ በኩል ልታጠምደው እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ እስካሁን እኔን አልደፈረችኝም እንጂ አንዳንዶቹን ለጎረምሶች እንደምታቃጥራቸው ሰምቻለሁ፡፡

እንዳገኘው የላከቺኝ ሰው አንድ ቀን በራፉ ላይ ቆሞ ከኔ ጋር የነበረ ልጅ ጋር አግኝተነው ስንተዋወቀው አዲስ መሆናችንን ስንነግረው የስልክ ቁጥሩን ሰጥቶን ነበር፡፡ እቤት ገብታችሁ ቡና ልጋብዛችሁ ሲለን አሁን እንቸኩላለን ብለን ሌላ ጊዜ እንመጣለን ብለን ነበር የተለያየነው፡፡ እውነተኛ ምክንያታችን ግን የአባይን መገንባት የሚቃወም ጸረ ልማት ነው ብላ ሴትዮይቱ ስላስጠነቀቀችን ችግር ውስጥ እንዳንወድቅ ነበር፡፡ የዚያን ቀን ከኔ ጋር የነበረውን ልጅ ሸኝቼው ተሸሽጌ ተመልሼ ችግሬን ባወራው ልቤ ፈልጎ ነበር፡፡ ግን ፈራሁ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ስለነበር ነበር ብቻዬን እንድሄድ የፈቀደችልኝ ትንሽ ነጻነት ተሰምቶኛል፡፡ እቤቷ ስብስባን በወያኔና ደርግ መሃል ያካሄዱትን የጦርነት ፊልም ጭንቅላታችን ውስጥ እየጠቀጠቀች ልታሳብደን ከደረሰው ይሄ ይሻለኛል፡፡

በተነገረኝ መሰረት እጄ እየተንቀጠቀጠ የበሩን ስልክ ተጭኘው ስጠብቅ በሩን ከፍቶ በእጁ ሰላምታ ሰጠኝ፡፡ እየተንተባተብኩኝ የጠበቃዬን ወረቀት እንዲተረጉምልኘ እንደሆነ የመጣሁት ነገርኩት፡፡ ግቢ ብርድ ነው ብሎኝ የምንቀጠቀጠው በብርዱ ብቻ መስሎት ማሞቅያውን ከፍ አድርጎ ጋቢ አመጣልኝ፡፡ ሻዩን ጥዶ የሃገሩን ቋንቋ እሱም ያን ያህል እንዳልሆነ አስረድቶኝ ከሞላ ጎደል የማውቀውን ደግሞ ተረጎመልኝ፡፡ ርህራሄውንና ሊረዳኝ የሚያደርገውን ትብብር ሳይ ያቺን ሰይጣን አለቃችንን ብቻ ሳይሆን እራሴንም ጠላሁኝ፡፡ የዋህነቱ ቅንነቱና ወገኑን ለመርዳት የሚያደርገውን ሙከራ ስገነዘብ በእውነት ስንት የሃገሬ ልጆች እንደበደልኩኝ ተሰምቶኝ ተንዘፍዝፌ ሳላውቀው እንባዬ በአራት ማእዘን መውረድ ጀመረ፡፡ ያገሬ ልጅ ተደናግጦ መሃረቡን አውጥቶ አዝኖልኝ የረጠቡ አይኖቹን ባንድ እጁ እያሻሸ አይዞሽ ይሄ ቀን ያልፋል ሁሉም መጀመርያ ተቸግሮ ነው እያለ ትከሻዬን እያሻሸ ሲያጽናናኝ ባሰብኝ፡፡                                                                                                                                      

 ከዘመዶችሽ የሰማሽው አዲስ ነገር አለ ወይስ ኬዝሽ ነው ያበሳጨሽ ብሎ አይን አይኔን ሲያይ አይኑን ፈራሁት፡፡ ለምን እንደመጣሁ እንደበፊቶቹ ሰዎች መድፈር አቃተኝ፡ ፡ በጭንቀት ሰውነቴ ውስጥ የነበረው ብርድ ወደ ሙቀት ተቀይሮ እጆቼን ሲረጥቡና በጀርብዬ ላቤ ሲከባለል ይበልጥ የሚያውቅብኝ መስሎኝ ልሳኔ ሁሉ ተዘግቶ በድን ሆንኩኝ፡፡ ፊቴን ለመተጣጠብ ወደ መጸዳጃ ቤት ገብቼ በሩን ቆልፌ በለቅሶ ያበጡ አይኖቼንና ፊቴን ስመለከት የወንጀለኛነት ስሜት ተሰምቶኝ እራሴን ማየት ጠላሁ፡፡ ገንዳው ጫፍ ቁጭ ብዬ ስንሰቀሰቅ ሰምቶኝ ኑሮ ነይ ብቻሽን አይደለሺም አይዞሽ ሲለኝ አንድ አፍታ ያቺ ሰይጣን የመጀመርያ ሴቲቱ ስልክ ደውላ አይዞሽ ብቻሽን አይደለሽም ያለችኝን አስታውሼ አረርኩኝ ደበንኩኝ፡፡                               

ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ አላገኝም ብዬ የምሰራውን ሁሉ ልዘረዝርለት ወሰንኩኝ፡፡ በዚህ መሃል ስልኬ አቃጨለ፡፡ ቁጥሩን ሳየው የዛች ሰጣን ስለነበር ተደናግጬ በስልኩ የምታየኝ መስሎኝ ስልኩን መሬት ላይ ለቀኩት፡፡ ስልኬ ተባበረኝ መሰለኝ ባትሪውና ስልኩ ተለያይተው እዛ ሲቢንቶ ላይ ተከሰከሱ፡፡ ሳነሳው መስታውቱ እዛው ላይ ደቆ ስባሪው አውራ ጣቴ ላይ ተሸንቁሮ ደሜ ኮለል ብሎ ወረደ፡፡ ቀኑ አስራ ሁለት የሚካኤል ቀን ስለነበር እዛች ሽንት ቤት ውስጥ ጥፋቴን በእራሱ መንገድ እያሳየኝ እንደሆን ገባኝ፡፡ ደሙ አልቆም ስላለኝ በሩ ላይ ሆኖ ለሚያጽናናኝ በሩን ከፍቼ ገንዳው ቧንቧውን ከፍቼ በጣቴ የሚደማውን ይዤ ማልቀሴን ቀጠልኩኝ፡፡

ምኑንም ያላወቀው ያገሬ ልጅ ተደናግጦ እራፊ ጨርቅ አምጥቶ ጠቅልሎ አስሮልኝ የተበታተነውን ስልክ ሰባስቦ ወደ የእንግዳ መቀበያው ይዞኝ ገባ፡፡ ብስጭት ያስረሳል ብሎ ወይን ቀድቶልኝ አጠገቤ ተቀምጦ እንደ ታላቅ ወንድም ትከሻዬን እያሻሸ የሚረብሽሽ ነገር ካለ ለመስማት ዝግጁ ነኝ ጤናሽስ እኔት ነው ያምሻል ወይ ሲለኝ ከባድ በሽታ እንደያዘኝ የጠረጠረም መሰለኝ፡፡ ለኔ የምትነግሪኝ ለቄስ እንደምትነግሪው አድርገሽ ውሰጅው ሲለኝ የማስበውን ሁሉ ያወቀብኝ መሰለኝ፡፡                            

ጣቶቼን እያፍተለተልኩኝና ጥርሶቼ እየተንገጫገጩ ልሰልለው እንደተላኩኝ ነግሬው ወደ በሩ ለመሮጥ ቃጣኝ፡፡ ምንም የመገረም ስሜት ሳያሳየኝ የሰይጣኗን ስም በቀጥታ ጠርቶ እሷ ነች አንቺንም የላከችሽ? አለኝ፡፡ እንዴት አወክ? ሌሎችስ እንዳሉ ማን ነገረህ? ብዬ እሱኑ ፈርቼ በእንባ የቀሉ አይኖቼን አፍጥጬ መልስ በፍጥነት መስማት ፈለኩኝ፡፡ ያጋመስኩትን ወይን እየሞላው ቀስ በይ አትቸኩይ፡፡ ወያኔ በየስርቻው የስደተኞችን ችግር በመጠቀም ወደ ተቃዋሚ ሰፈር ገብተው እንዳይታገሉ በጀት መድበው አንድ ለአምስት እያሉ የምታሰባስባቸውን እንሰማለን እናውቃለን፡፡                                                                                     

ብዙዎቹም

ከሃገር ውስጥ ተመልምለውና ተመክረው ሰልጥነው የሚመጡ ናቸው፡፡ አንቺ እንዳለሽበት ጊዜያዊ ካንፕ ደግሞ ወደ ሃገር ሲመለሱ እንደሚፈሩ ወያኔ ስለምታውቅ ሆዳሙን በጥቅም ፈሪውን ስም እያስጠፋችና እያስፈራራች እየመለመለቻቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋናው የወያኔ እቅድ የተቃዋሚውን ሰፈር ከፋፍሎ ለማዳከምና ተሰሚነት ያላቸውን ግለሰቦች በመነጠል አንገታቸውን ለማስደፋት ነው፡፡ እኛም ለችግር ብለው የሚጠጓቸውንና ለጥቅም ብለው ወደ እነሱ እየተጠጉ ስደተኛውን የሚሰልሉትን ለይተን ብዙዎቹን እናውቃለን፡፡ አንቺን እንድትሰልዪ እንደላኩሽ ተቃዋሚውም እንደ አቅሙ እንዳንቺ ተቸግረውና ተገደው በተመለመሉና ወገናቸው ምንም ውስጥ ሆነው መርዳት በሚፈልጉ ሃገር ወዳዶች ውስጣቸው አዘጋጅተን እንከታተላለን፡፡ ስለ አንቺም ሆነ ስለሌሎቹ ሰምተናል፡፡ብሎ ምንም የማያውቁት ጉዳይ እንደሌለ እውነት የሆነ ነገር ዘርዝሮ ሲነግረኝ ፈዝዤ ቀረሁ፡፡

አንዴ ተሳስተሽ ከገባሽበት ጣጣ ውስጥ ለመውጣት አሁን እንደምትነግሪኝ ከነሱ መሸሽ ሳይሆን አንዴ ገብተሽበታል እዛው መቆየት ነው፡፡ እነሱ መስማት የሚፈልፈልጉትን እየነገርሻቸው እራስሽንም ሆነ ሌሎችን ላደጋ ሳታጋልጪ ከእኛ ጋር እየተመካከርሽ የተገላቢጦሽ እራሳቸው ላይ መስራት ይቻላል፡፡ በሰው ሃገር ውስጥ ተቀምጦ ስደተኛን መሰለልም ሆነ መጉዳት ከባድ ወንጀል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ብዙ መረጃዎችና ምስክሮች ማሰባሰብ አለብን፡፡ አሁን ተንኮሉ ገብቷቸው እንዳንቺ ወደ ወገን ሰፈር እየመጡ ያሉ ብዙ ናቸው፡፡ ይህንን ሁሉ ሚስጥርሽን ካወቁ ቦኋላ ወዲያው ብታስደነግጫቸው በስደተኛ ጥያቄሽ ሊጎዱሽ ይችላሉ፡፡ብሎ ብዙ ጠቃሚ እዚህ ልገልጸው የማልሻ ምክሮች መክሮ ሞራል ሰጠኝ፡፡                      

ባላሰብኩትና ባልጠበኩት መንገድ ወገኔን የምረዳበትና ሳላውቅና ሳይገባኝ ወገኔን ለግል ጥቅም ብዬ የከዳሁትን ማካካሻ መንገድ ከፍቶልኝ ለአንድ አመት ከሁለት ወር ከሌሎችም እንደ እኔ ተሳስተው ከነበሩ ጋር በሚስጥር እየተገናኝን የተቃዋሚውን ወገን ስተባበር ቆይቼ ፈጣሪዬም ታረቀኝ መሰለኝ የመኖርያ ፈቃዴ ተስተካከለልኝ፡፡ በየካንፑ ለቀሩት ጓደኞቼ ደህንነት ስል ዝርዝር ጉዳዩን ለጊዜው አልነግራችሁም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ወያኔይቱን ሸሽተን መጣን ብለው ስደተኛውን የሚሰልሉና ይህንን ጨቋኝ መንግስት የሚረዱትን በተለይ ዋናዎቹን በደንብ ተለይተው ይታወቃሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

በሰው ሃገር ውስጥ ሆኖ ስለላ ማካሄድ ይቅርታ የሌለው ወንጀል ስለሆነ የሚመለከታቸው ሃገር ወዳዶች ከሃገሩ መንግስታት ጋር ሃገር ወዳዶችና የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እየሰሩበት እንደሆነ አንዳን ፍንጮችና ውጤቶች እየታዩ ስለሆነ የሚጋለጡበት ጊዜ እሩቅ አይደለም፡፡ ምናልባት እንደ እኔ ሳታውቁ ወይም ለትናንሽ ጥቅማ ጥቅሞች ብላችሁ ህሊናችሁን ላቆሸሻችሁ በጊዜ እንደ እኔ ወገናችሁን በመርዳትና የመረጣችሁትን የተቃዋሚ ድርጅት በመተባበር የተግባር ንሰሃ ግቡ፡፡                            

በተለይ እናንተ ሃገር ውስጥ ወያኔይቱ በደለችን ብላችሁ የስደት ፈቃዳችሁን በማጭበርበር አግኝታችሁ አሜሪካና አውሮፓ አውስትራሊያ አፍሪካን ጨምሮ በመላው አለም የተደላደለ ኑሮ እየኖራችሁ ስደተኛን ለምትሰልሉበትና ለምትከፋፍሉበት ደሞዝ ሃገር ውስጥ የባንክ አካውንት ከፍታችሁ እንደሚከፈላችሁ ይታወቃል፡ ፡ በየቤተክርስቲያኑ ምእማናኑን የምትከፋፍሉ፡፡                             

በየፌስ ቡኩና በየየፓልቶክ ክፍሎች ስማችሁን እየቀያየራችሁ በወገኖቻችን ላይ ፍዳውን የምታራዝሙ ወደ ፊት በህግ ብቻ የምንፋረዳችሁ ሳይሆን እስከዛው ዘመድ ወገኖቻችሁ እንዲያውቁዋችሁ ትክክለኛ ስማችሁንና በመረጃ የደገፈ ስራችሁን በየተቃዋሚው ድህረ ገጾች ማውጣቱ ይቀጥላል፡፡ ወደ ሃገር በሚተላለፉ የየቴሌቪዥንና የራዲዮ ፕሮግራሞች ስማችሁ እንደሚወጣና ፎቶዋችሁ ተሰራጭቶ መቀጣጫ ትሆናላችሁ፡፡ ዘመዶቻችሁም ማንነታችሁን አውቀው ጥንቃቄ ይወዳሉ፡፡ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሰርታችሁ ያመጣችሁት ንብረት ይመስል ከህዝብ እየዘረፋችሁ የምታከማቹት ንብረት ቤትና ንግድ እመኑን አትበሉትም፡፡                                                                                                                                         

በየትኛውም ማእዘን ያሉ ጥቂት የማይባሉ ለሃገራቸው የሚቆረቆሩ ወገኖች እያንዳንዷን በህዝብ ደም የምታሰባስቡትን ንብረትና ለምታደርሱት ጥፋት ይመዘግባል፡፡ ለዚህም የምትከፍሉት ዋጋ ከባድ ይሆናል፡፡ ከዚህ ከሚመጣባችሁ መአት ለመዳን ዛሬ ነገ ሳትሉና ሳታመነቱ እራሳችሁን የአንባ ገነኖች መጠቀሚያ ከመሆን ታቀቡ፡፡ ህዝባችን ይቅርታ አድራጊና መሃሪ ነው፡፡ በጥፋታችሁ ተጸጽታችሁ ቀኑ ሳይመሽ ወደ የህዝብ ጎራ መቀላቀል ይበጃችኋል፡፡ አሊያ ከማይቀረውና አድምኖ ከሚመጣው የሕዝብ የነውጥ ማእበል አትተርፉም፡፡

የህንን በእውነተኛ ድርጊት ላይ የተመሰረተ መረጃ በባለታሪኳ ፈቃድና ተባባሪነት ሲቀርብ ለባለታሪኳና ለሌሎች በሷ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ደህንነት ተብሎ የመዝጋቢውን ስም ጨምሮ ብዙ ነገር ተውጠዋል፡፡ የበለጠ መረጃ ለማሰባሰብ የሰዎችና የቦታወች ስም አልተካተቱም፡፡ ነገሩ በሂደት ላይ ስለሆነ አንድ አንድ የተነገሩ አሰቃቂ ተግባሮችን ለተለየ ምክንያት ተብሎ አንዳይጠቀሱ ሲደረግ ታሪኩ ተቀንጭቦ እንዲወጣ የተደረገው በባለታሪኳ ቁጭትና ግፊት ነው፡፡ ወደፊት ነገሮች መስመር ሲይዙ ታሪኩ ምንም ሳይቀነስና ሳይጨመር ከባለታሪኳ በቀጥታ ትሰሙታላችሁ፡፡
ለወገናችን መቆም ባንችል ስቃዩን ከሚያበዙበት ጎን አንሰለፍ፡፡ 

No comments:

Post a Comment