Tuesday, July 8, 2014

ሕወሓት ውጥረት ውስጥ ናት፤ ከሰማያዊ ፓርቲ የሺዋስ አሰፋን፤ ከአንድነት ሃብታሙ አያሌውን አሰረች



(ዘ-ሐበሻ) የሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተዳደር በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ታወቀ። ከየመን የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አፍና ከወሰደች በኋላ ከሃገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በሚደርስባቸው ጫና በመበርገግ ላይ እንደሚገኙ ከድርጊታቸው እንደሚያስታውቅ የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ በዛሬ ዕለት ከመኖሪያ ቤታቸው የተወሰዱት አቶ የሺዋስ አሰፋና ሐብታሙ አያሌው ጉዳይም ከዚሁ ውጥረት ጋር በተያያዘ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።
yeshiwas
habtamu ayalew
የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆነው አቶ የሺዋስ አሰፋን በብዛት የሚቆጠሮ የደህነነትና የፌደራል ፖሊሶች የመኖሪያ ቤቱን በመክበብ ቤቱን ሰብረው የገቡ ሲሆን እጁን በካቴና ጠፍረው ቤቱን እንደበረበሩት ከአዲስ አበባ ለዘ-ሐበሻ የመጣው መረጃ ያመለክታል። ደህነንቶቹ አቶ የሺዋስን ወደ ማዕከላዊ አስረው ከወሰዱ በኋላ ወደ ማ ዕከላዊ ምርመራ እንደወሰዱት ሲታወቅ ከቤቱ በርካታ ንብረቶችን ይዘው እንደሄዱም ለማወቅ ተችሏል።
እንደ ደረሰን መረጃ ከሆነ የሰማያዊ ፓርቲው አቶ የሺዋስ በሚበረበሩበት ወቅት ባለቤቱ ጭምር ወደ ውስጥ እንድትገባ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ከመኖሪያ ቤቱ ወደ አንድነት ፓርቲ ጽህፈት ቤት በመጓዝ ላይ የነበረው አቶ ሃብታሙ አያሌው ቦሌ ደንበል ህንጻ አካባቢ ብዛት ባላቸው የደህነት አባላትና የፌደራል ፖሊሶች መንገዱን በመዝጋት ይህን ወጣት የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል ይዘውት ወዳልታወቀ ስፍራ ሄደዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አቶ ሃብታሙን አስሬያለሁ፤ እዚህ ነው ያሉት ያለ አካል ባይኖርም አንድነት ፓርቲ የአባሉን መታሰር አረጋግጧል።
የእነዚህን ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በድንገት መታሰር በማስመልከት ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም በፌስቡክ ገጹ የሚከተለውን አስተያየት አስፍሯል።
“ህወሃት በትጥቅ ትግል የሚታገሉትን ካሰረ ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትንም ካሰረ፣ በእስክርቢቶ የሚታገሉትንም ካሰረ፣ በጸሎት የሚታገሉትንም ካሰረ እንግዲህ ማን ቀረው? ህወሃት ትግል የሚባል ነገር አልፈልግም ብሎአል። ሺ ዓመት እየቀጠቀጠ ለመግዛት ያልማል። ይህንን ህልመኛ ቡድን ለማስወገድ በሁሉም የትግል መንገዶች የሚታገሉ ሃይሎች እጅና ጓንት ሆነው በአንድነት መነሳት ለነገ የማያሳድሩት የቤት ስራ ነው። አንድነት፣ ሰማያዊ፣ መኢአድና መድረክ እጅ ለእጅ ሆነው ሰላማዊውን ትግል መጀመር፣ ግንቦት7፣ አርበኞች ግንባር፣ ኦነግና ትህዴን ( ደሚት) አንድ ላይ ሆነው ደግሞ የትጥቅ ትግሉን መጀመር አለባቸው። ጥቃቅን ልዩነቶቻችን ይህንን የሰፈር ጎረምሳ ካባረርነው በሁዋላ ይፈታሉ። ለየሽዋስ ያልሆንክ የሰማያዊ አባል፣ ለአንዱአለምና ለሃብታሙ ያልሆንክ የአንድነት አባል፣ ለአንዳርጋቸው ያልሆንክ የግንቦት7 አባል፣ ለበቀለ ገርባ ያልሆንክ የመድረክ አባል፣ ለአቡበክር ያልሆንክ ሙስሊም ምእመን፣ ለዞን ዘጠኝ ያልሆንክ ጦማሪ፣ ለእስክንድር ያልሆንክ ጋዜጠኛ፣ ለርእዮት ያልሆንክ መምህር ከእንግዲህ ለራስክም አትሆንም።
ትንሽ ወይም እስከመጨረሻው ሞተን ነጻነት በአገራችን ምድር ይወለድ።

No comments:

Post a Comment