Thursday, July 3, 2014

በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ… ኤርትራ እና የመን ተፋጠዋል

 

ኤርትራ የየመንን አየር መንገድ እንደምትዘጋ አሳወቀች (ምክንያቱ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰር ነው)
(ኢ.ኤም.ኤፍ) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰና፣ የመን ውስጥ በየመን የጸጥታ ሃይሎች ታፍኖ መታሰሩ ብሎም አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አለመታወቁ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን ላይ ትራንዚት እያደረገ በነበረበት ወቅት ነበር በየመን ታጣቂዎች ታፍኖ የተወሰደው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በየቦታው ድምጻቸውን ለማሰማት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ከ’ነዚያ ሁሉ ድምጾች ግን ጎልቶ የወጣው በኤርትራ በኩል የተላለፈው መግለጫ ነው። ይህን የኤርትራን መግለጫ መሰረት በማድረግ፤ ሌሎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የራሳችንን ሃሳብ እንሰጣለን።
ኤርትራ ለየመን በላከችው መልዕክት መሰረት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ካልተፈታ፤ በኤርትራ አየር ላይ የሚሄዱትንም ሆነ፤ ምድር ላይ የሚያርፉት የየመን አውሮፕላኖች የሚታገዱ መሆኑን ገልጿል። ይህ ደግሞ እያደገ ለመጣው የየመን አየር መንገድ ትልቅ ኪሳራን የሚያስከትል ነው። ኤርትራ የጀርመኑን ሉፍታንዛ ካገደች ወዲህ፤ የየመን አየር መንገድ ሉፍታንዛን ተክቶ፤ አስመራ ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛል። በዚህም መሰረት ወደ አውሮፓ የሚሄዱም ሆኑ የሚመጡ አውሮፕላኖች በየመን በኩል አድርገው ማለፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። አሁን ኤርትራ የየመን አየር መንገድን እንደሉፍታንዛ የምታገድ ከሆነ፤ የየመን መንግስት የሚያገኘው ከፍተኛ ገቢ ሊቀንስበት ይችላል።
ከዚህ በፊት ባቀረብነው ዘገባ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእንግሊዝ አገር ዜግነት ያለው እና የእንግሊዝን ፓስፖርት ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ስለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስናወራ፤ የ እንግሊዝንም መንግስት የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል። እንግሊዝ ዜጋዋ በየመን ታስሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይላክ በአውሮፓ ዲፕሎማሲያዊ ስራ መስራት ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ እና የመን እስረኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ቢኖራቸውም፤ የመን የ እንግሊዝ ዜግነት ያለውን ሰው አሳልፋ እንዳትሰጥ በዛቻ ሳይሆን፤ በህጋዊ መንገድ የመንን መሞገት ያስፈልጋል።
ከ እንግሊዝ በተጨማሪ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ ማድረግ ሌላው ብልሃት ነው። አሜሪካ ከየመን ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት በመጠቀም አቶ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ በየመን የአሜሪካ ኢምባሲ ጥረት እንዲያደርግ ጫና መፍጠር ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ግንቦት ሰባት የሚያወጣቸው የማስፈራሪያ መግለጫዎች ድምጸታቸውን በማስተካከል እንደአንድ በሳል የፖለቲካ ድርጅት የሚታይ ዲፕሎማሲያዊ ስራ በመስራት ለውጤት መብቃት አለባቸው። በመሆኑም ከማስፈራሪያ መግለጫዎች ይልቅ፤ ከዲፕሎማሲያዊው ዘመቻ ጎን ለጎን… ህጋዊ ጠበቃ በየመን አዘጋጅቶ፤ ጉዳዩ በኢሚግሬሽን እና በዋናው ፍርድ ቤት እንዲታይ በማድረግ፤ ቢያንስ አቶ አንዳርጋቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይላክ ጊዜ መግዛት ይቻላል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው እንደመሆኑ መጠን ዲፕሎማሲያዊው ዘመቻ በእንግሊዛውያን ጭምር እንዲሰራ፤ ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ሚዲያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ተገቢ ነው። የምናወጣቸውም መግለጫዎች በአማርኛ ሳይሆን ሁሉም አገራት በሚረዱት እንግሊዘኛ ቋንቋ ሊሆን ይገባዋል። ከዚያ ውጪ ግን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባስቸኳይ ካልተፈታ በኢትዮጵያ እና በየመን ባለስልጣናት ላይ እርምጃ እንወስዳለን” አይነት መግለጫዎች፤ ወያኔ ኢህአዴግ “ግንቦት ሰባት የአሸባሪዎች ድርጅት ነው” የሚለውን አባባል ከማጠናከር ውጪ ብዙም ፋይዳ ላይሰጥ ይችላል።
ይህ ብቻም አይደለም። በማህበራዊ ድረ ገጾች እና ሌሎች ሚዲያዎች ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከዚህ በፊት ያደረጓቸው ንግግሮች እየተለጠፉ መሆኑን ታዝበናል። እንዲህ አይነቶቹ… ቀደም ሲል የተደረጉ ንግግሮችን አሁን ለእይታ ማቅረቡ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እስሩ እንዲጸናባቸው እንጂ፤ እንዲፈቱ ስለማይረዳቸው፤ በዚህ ረገድ ሌላ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በድጋሚ ለማሳሰብ ያህል… ግንቦት ሰባትም የማስፈራሪያ መግለጫዎችን ከማውጣት ይልቅ፤ በሌሎች ዜጎች እየተደረጉ ያለውን ጥረት ማስተባበር እና ዲፕሎማሲያዊ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረግ አለበት። ኤርትራ ያደረገችውን ውሳኔ በማድነቅ፤ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ማበረታታት ከግንቦት ሰባት አመራሮች የሚጠበቅ ነው።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው መሆኑን፣ ንብረታቸው በወያኔ ኢህአዴግ መወረሱን፣ ወላጅ አባታቸው እና ቤተሰባቸው በእስር መንገላታቱን አጉልቶ በማውጣት የወያኔ ኢህአዴግን አስከፊ ገጽታ ማሳየት ይቻላል። አሁንም የየመን መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ወደ ኢትዮጵያ ብትመልስ በወያኔ ኢህአዴግ ሊደርስባቸው የሚችለውን የግድያ ወንጀል ማሳወቅ እንጂ፤ “አቶ አንዳርጋቸው ካልተፈታ ወዮላቹህ!” የሚለው አይነት ማስፈራሪያ ህሊና ለሌላቸው የሁለቱም አገራት አምባገነን መሪዎች ላይሰራ ይችላል። ህዝብ እና አገር የሚመሩት በእውቀት እና በጥበብ ጭምር በመሆኑ፤ ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመከተል… ነገር ግን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አቶ አንዳርጋቸውን የማስፈታቱን ሂደት እንቀጥል – የዛሬው ዜና መልእክታችን ነው።

No comments:

Post a Comment