Monday, July 7, 2014

የአሸባሪነት ሕግና እኛ

የአሸባሪነት ሕግና  እኛ 

terrorism


የግንቦት ሰባቱ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በዚያ ኢትዮጵያዊያኑን በሚበላው ምድርና በሚበሉት አራዊት ከአካላቸው በስተቀር የሰውነት መገለጫ በሌላቸው ማሰብ የሚባል ነገር በማያውቁት ዘገምተኞች እጅ ሲታገትና በኋላም ተላልፎ ተሰጠ ሲባል ይሄንን ድንገተኛ አሳዛኝና ልብ ሠባሪ ዜና የሚገልጹትን ይዞች (ሊንኮች) እንዳየሁት ተጋርቸ (ሼር አድርጌ) በመጽሐፈ ገጼ (በፌስቡኬ) ለጠፍኩት (ፖስት አደረኩት) በማግስቱ አንድ ወዳጀ ምን ይለኛል? ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄንን ዜና ፖስት ያደረገ (የለጠፈ) አንተ ብቻ ሳትሆን አትቀርም አለኝ፡፡ አንተስ አላደረከውም? ስል ጠየኩት የለበጣ ፈገግታ እያሳየኝ “አዬ አንተ! ይሄንን ማድረግ በአሸባሪነት ሊያስከስስ እንደሚችል አታውቅም?” ሲለኝ እየቀለደ መስሎኝ ነበር በኋላ ላይ ኮስተር ብሎ “ቆይ! ምን አስበህ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርክ እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ? በገዛ እጅህ እኮ ገመዳቸው ውስጥ ገባህላቸው” ምንትስ ሲለኝ የምሩን እንደሆነ ገባኝና የትኛው ሕግ ነው ይሄንን የሚለው? ስል ጠየኩት፤ የቻለውን ያህል ይሄ አገዛዝ (ወያኔ) “የአሸባሪነት ሕግ” ሲል ያወጣውን አስቂኝና አስገራሚ ሕግ አስረዳኝ፡፡ ሕጉ ሥራ ላይ እንደዋለም በብዙኃን መገናኛ ተገልጾ እንደነበረ ነግሮኝ እንዴት ግንዛቤው ሳይኖረኝ እንደቀረ ተገርሞ ጠየቀኝ፡፡ ቶሎ ብየም የለጠፍኩትን እንዳጠፋ መከረኝ፡፡
በእርግጥ ዝርዝሩን ባላውቀውም “የአሸባሪነት ሕግ” እያሉ ሲጠቅሱትና ዜጎች እየተወነጀሉ ወህኒ ሲወርዱማ እሰማለሁ፡፡ እንግዲህ አንዳንዴ ለመንፈሳዊ ጉዳይ ለሳምንታት ለወራት ወደ ገዳም ወጣ የምልባቸው ጊዜያት አሉና በዚህ ወጣ ባልኩበት አጋጣሚ ሳልሰማቸው ከምቀራቸውና ካመለጡኝ ጉዳዮች አንዱ ነው ማለት ነው ስል መለስኩለት፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች እንዲያውም “እንዴ መቸ?” እያልኩ የምጠይቅባቸው ጉዳዮች ይበዙብኛል፡፡
ለማንኛውም እሱ እንዳለኝ ከሆነ “ግንቦት 7” በአገዛዙ በአሸባሪ ድርጅትነት ተፈርጇልና እንደ ሕጉ ስለዚህ ድርጅትና ስለ አመራሮቹ ምንም ዓይነት መረጃ ቢሆን መቀበልና መስጠት ማስተላለፍ፣ ማንኛውንም ዓይነት እርዳታና ድጋፍ ማድረግ በአሸባሪነት አስወንጅሎ እንደሚያሰቀጣ አስገንዝቦኛል፡፡
አሀ! ይሄንንማ ከአንባቢያን ጋራ ነው ላወራው የሚገባ ብየ ለአገዛዙም ላቀርባቸው የፈለኳቸው እንደ ዜጋ ሊመለሱልኝ የሚገቡ ጥያቄዎች አሉና ወደ እናንተ አመጣሁት፡፡ በጣም ይገርማል ለካ ለዚህ ኖሯል ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችና ምዕራባዊያን መንግሥታት ይህ የአሸባሪነት ሕግ የራሱን ሕገ መንግሥት፣ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን፣ የተለያዩ ዓለም ዓቀፋዊ ድንጋጌዎችንና ስምምነቶችን ይቃረናል ይጥሳል ማለታቸው? በጣም ይገርማል፡፡
እዚህ ላይ ለአገዛዙ ጥያቄ ማንሣት እወዳለሁ “ግንቦት 7” አሸባሪ የተባለው ምን አድርጎ ነው? የሚያሸብረውስ ማንን ነው? በንጹሐን ዜጎች ላይ የፈንጅ ጥቃት የፈጸመበትና ለመፈጸም የዛተበት ጊዜ አለ ወይ? የድርጅቱ የትግል ዓላማ ማዕከል ያደረገው ምን ሆኖ ነው በአሸባሪነት ያስፈረጀው? የድርጅቱ ዓላማ አንድን ሃይማኖታዊ ወይም ጽንፈኛ የግል ወይም የቡድን አቋም ወይም አስተምህሮ በሕዝቡ ላይ በግዳጅ ለመጫን ለማስረጽ ነው ወይ? እናንተ እንዳላቹህት ሁሉ የኢትዮጵያም ሕዝብ  ግንቦት ሰባትን በአሸባሪነት መፈረጅ ካለበት የግድ በእነኝህ በጥያቄ መልክ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ መኖሩን እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል፡፡ አገዛዙ እነኝህን ጥያቄዎች ያለ እብለት በግልጽ ለሕዝቡ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ ይሄንን ማድረግ ካልቻለ ግን ስም ማጥፋት ነውና ያንን “የአሸባሪነት ሕግ” ስትሉ ያወጣቹህትን ኢፍትሐዊ “ሕግ” የመቀበልና በእሱም የመገዛት ግዴታ አይኖርበትም ማለት ነው፡፡ እናንተ ስላላቹህ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዚያ ብሎ የሚያምን ይመስላቹሀል? እርግጠኛ ነኝ የፈለጋቹህትን ብትሉ እንደዚያ ብሎ ያምንልናል ብላቹህ እንደማታስቡ፡፡ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያላቹህን ቦታ አሳምራቹህ ታውቃላቹህና፡፡ እድሜ ዘመናቹህን እራሳቹህን እንዳጃጃላቹህ አላቹህ፡፡ የዚህ “ሕግ” ኢፍትሐዊነት ከላይ እንዳየነው ከአመክንዮ (ከሎጂክ) እና ከተለያዩ ድንጋጌዎች አንጻር ሲታይ ብቻ አይደለም ከሃይማኖትም፣ ከባሕልና ወግም አንጻር ሲታይም ጭምር እንጅ፡፡
ይህ የአገዛዝ ሥርዓት ከምዕራባዊያን መንግሥታትና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች “የተቃውሞ እንቅስቃሴንና አሸባሪነትን ለያይቶ አያይም በጣም በተሳሳተ መንገድ አንድ ላይ ደባልቆ ይፈርጃል ” እያሉ ለሚያቀርቡበት ክስ ደባልቄ አላየሁም አላይምም ይላልና እንግዲያው እንዲህ ከሆነ በዚህች ሀገር ያሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችና አንቀሳቃሻቸው እነማን ናቸው??? ከጋዜጠኞች እስከ ፖለቲከኞች ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እስከ የሃይማኖት መሪዎች በአሸባሪነት ወንጅሎና ፈርዶ ወህኒ እየወረወረ ያለው ማን ነው? እንግዲህ እንደ ሕጋቹህ ሁሉ እነዚህን በሐሰትና በፈጠራ በአሸባሪነት ተወንጅለው ወይም መብታቸውና የዜግነት ግዴታቸው የሆነውን ትግል በመታገላቸው ወህኒ የተወረወሩትን ወገኖች መጠየቅ መጎብኘት መርዳት በአሸባሪነት ያስፈርጃል ያስወነጅላል ያሳስራል ማለት ነዋ?
የአሸባሪዎች ሕግ ከሃይማኖት አንጻር፡-
እኔ እንግዲህ ክርስቲያን ነኝ፡፡ እንደ ክርስቲያንነቴም እድን ዘንድ ክርስቶስ እንዳደርግ ያዘዘኝ ትዕዛዝ አለ፡፡ በወንጌሉ ላይ ሉቃ. 10፤25-37 ያለ አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ “ እነሆም አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ መምህር ሆይ! የዘለዓለም ሕይዎት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው፡፡ እሱም በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው፡፡ እሱም መልሶ ጌታ አምላክህን በፍጹም ኃይልህም በፍጹም ሐሳብህም ውደድ አለው፡፡ እውነት መለስክ ይሄንንም አድርግ አለው፡፡
እሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወዶ ኢየሱስን ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ እነርሱም ደግሞ ገረፉት ደበደቡትም በሕይዎትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ፡፡ ድንገትም አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፡፡ እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፡፡ አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፈስሶ አሰራቸው በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው ጠበቀውም በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና ጠብቀው ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሀለሁ አለው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሀል? እሱም ምህረት ያደረገለት አለ፡፡ ኢየሱስም ሒድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው፡፡” ይላል ቃሉ፡፡
ታዲያ እንግዲህ እኔም እንደ ክርስቲያን እድን ዘንድ ቃሉ እንዳዘዘኝ ሁሉ የዘር የሃይማኖት የአመለካከት ልዩነትን ሳላደርግ ዘሩ ሃይማኖቱ አመለካከቱ ወይም አስተሳሰቡ የራሱ ነውና ያንን አክብሬ በሰውነቱ በወገንነቱ በወንበዴ እጅ ወድቆም ይሁን ችግር ደርሶበት ለተቸገረ ወገኔ ባዝን አቅም ካለኝም ከደረሰበት አደጋ ወይም ችግር እንዲድን ብረዳው ሥርዓቱ በአሸባሪነት ሕጉ መሠረት ለምን ሃይማኖታዊ ግዴታህን ተወጣህ ብሎ በአሸባሪነት ወንጅሎ ሊቀጣኝ ነው? እኔስ ይሄንን ፈርቸ የጌታየን ቃል አለማክበር ይኖርብኛል? እንዲህ ካደረኩስ የክርስቶስ ፍቅር በውስጤ አለ? ክርስቲያንስ ነኝ ማለት እችላለሁ? እንዲህም ብሎ ክርስትና የለ! በሉ አርፋቹህ ተቀመጡ እራሳቹህን ነው የምታጃጅሉት ሌላ ማንንም አይደለም፡፡ እንዲህ የምታስቡና የምትኖሩም ካላቹህ ክርስቲያን ነኝ እንዳትሉ አይደላቹህምና፡፡
በእውነት ለመናገር በዚህች ሀገር ለክርስቶስ ያደሩ መልካም እረኞች እውነተኛ የሃይማኖት አባቶች (መሪዎች) ቢኖሩ ኖሮ የዚህ ሕግ ተብየ የመጀመሪያ ተቃዋሚዎች እነሱ በሆኑ ነበር? “ጽድቁ ቀርቶ አሉ” አብረው እየዶለቱ ሕዝቡን የሚያስጨንቁ መለካዊያን ተኩላና ይሁዳ እነሱ አይደሉም እንዴ? ምእመናን ሆይ! ተስፋ ቁረጡ ለአምላክ ያደሩ ስለ በጎቹ እራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ አባቶች ያላቹህ እረኞች ያላቹህ እንዳይመስላቹህ ምንደኛና ነጣቂ ተኩሎች እንጅ፡፡
የአሸባሪነት ሕግ ከባሕላችንና ወጋችን አንጻር፡-
ስለ እውነት ለመናገር በጣም ደገኛ ባሕል ነበረን አለንም ምንም ዓይነት ልዩነት አለመግባባት ይኑረን በችግር ጊዜ ግን የራሴ ይቅርብኝ ብሎ እስከመደጋገፍ የሚደርስ፡፡ እንግዲህ በዚህ “ሕግ” መሠረት ወያኔ በራሱ ቡድናዊ ጥቅሙ ምክንያት ከወነጀላቸው ዜጎች ጋራ ኃዘንን ጨምሮ ሠርግ ማኅበር ክርስትና ቡና መጣጣት ወዘተ. የተከለከለ ነው ማለት ነው? አገዛዙ ስለጠላቸው ብቻ ጠላቶቻችን እንዳልሆኑ እያወቅን ከአጠቃላይ የማኅበራዊ ሕይዎት መስተጋብር ማግለል አለብን ማለት ነው?
ቆይ ቆይ ቆይ ቀይ መስቀል ከዚህ “ሕግ” በኋላ እንዴት ነው እየሠራ ያለው? ነው ወይስ ለቅቆ ወጥቷል? እንደምታውቁት ቀይ መስቀል ለሚሰጠው ሰብአዊ አገልግሎት በዘር በሃማኖት በማንኛውም ዓይነት የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነት ያልተገደበ ዓለማቀፋዊ በሆነ መርሑ መሠረት አገልግሎት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ በዚህ “ሕግ” መሠረት ቀይመስቀልም ሰብአዊነት በተሞላው መርሑ ሳቢያ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች አገልግሎቱን በሚሰጥበት ጊዜ በአሸባሪነት ሊከሰስ ነው ማለት ነው? ምንድን ነው እያወራቹህኝ ያለው? ወያኔ በቀዘነና በቃዠ ቁጥር ከሰብአዊ መብቶች፣ ከዓለማቀፋዊ ስምምነት ድንጋጌዎች፣ ከባሕልና ሃይማኖት ከገዛ ሕገ መንግሥቱም ሳይቀር የሚቃረን የሚጣረስ የአውሬና አረመኔያዊ ቡትቶ በቸከቸከ ቁጥር ሐግ እያልን ልንቀበል ነው እንዴ? ይሄ ሕግ ተብየው የሚያስጠብቀውስ ጥቅም የማንን ነው? የሀገርን? የሕዝብን? ወይስ ጥቂቶችን ብቻ ያቀፈውን ቡድን ጥቅም? ጉዳዩ በጣም ግልጽ ነው ሕጉ የሚያስጠብቀው የሀገርንና የሕዝቧን ሳይሆን የቡድንን ነው፡፡ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ግን ለአደጋ ይዳርጋል፡፡
ጥሩ እንግዲያውስ ቅዱስ ቃሉ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” የሐዋርያት ሥራ 5፤29 ይላልና እኔ በበኩሌ የፈለጋቹህትን አድርጉ ይሄንን ስትደነብሩ ስትንቦቃቦቁ ስትቀዝኑ ስትንቀጠቀጡ ስትሸበሩ ስትቀዝኑ የሞነጫጨራቹህትን ፀረ ሃይማኖታዊ ሕግጋት፣ ፀረ ወገወና ባሕል፣ ፀረ ሰብአዊ መብት፣ ፀረ ሰብአዊ መብቶች የሆነውን የጫካ የአውሬ “ሕግ” ቡትቶ አልቀበለውም ቀቅላቹህ ብሉት፡፡ ዜጎችን በግዳጅ እኔ እንደማስበው ካላሰባቹህ ብሎ ማሰብና ተፈጥሯዊና ሰብአዊ መብቶችን፣ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ መብቶችን መንፈግ ወንጀል ነው፡፡ መንጋ ወንጀለኛ ሁሉ እደግመዋለሁ ቀቅላቹህ ብሉት አልቀበለውም፡፡ ግንቦት 7 አይደለም ሌላም ይሁን ብቻ ሰው ይሁን እጠይቀዋለሁ እጎበኘዋለሁ በችግሩም እረዳዋለሁ እሄንን የማደርገው የግንቦት 7 አባል ስለሆንኩ አይደለም ልብ አድርጉ አባል አይደለሁም ሃይማኖታዊ ባሕላዊ ሰብአዊ ግዴታየ ስለሆነ እንጅ፡፡ ይሄ አሸባሪነት ነው ካላቹህ አንድ ሽህ ጊዜ ልሁን፡፡
ወንድ ከሆንሽ ልብ ካለሽ ዙሪያውን የሐገሪቱን አጎራባች ሀገራት ፍጹም መንግሥት ነኝ ከሚል አይደለም ከተራ ዜጋ እንኳን በማይጠበቅ ክህደትና ነውረኝነት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች መሬት ቆርሶ ከመስጠት አንስቶ በስደት ያሉትን ዜጎቻችንን ሕይዎትና ክብር ለባዕዳን መጫወቻነትና ለግፍ  አሳልፈሽ እየሰጠሸ በወዳጅነት ሳትይዥ ተቃዋሚዎች ሌላው ሁሉ ቀርቶ አንቺ ከሱዳን ስታገኝው የነበረውን ያህል ሁለንተናዊ ድጋፍ እንኳን ባይሆን መንደርደሪያ ቦታ ብቻ እንኳን እንዳያገኙ ሳትከላከይ አትፋለሚም ነበር? አይደለም 24 ዓመታት መንፈቅ እንኳን እንደማትቆዪ ታውቂዋለሻ፡፡ ወንድነት ማለት ጀግንነት ማለት እሱ ነበር እንጅ ነውረኛ በሆነ “በእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የአሕያ አስተሳሰብ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም በቡድን ጥቅም በመለወጥ የሥልጣን ዘመንን ለማራዘም መቃተት መንፈራገጥ አይደለም፡፡ ደሞ እኮ አያፍሩም እንደ ወንድ ይፎክራሉ ይወነናሉ ጉራቸውን ይነፋሉ፡፡ ሳትዋጋ የእግር መንገድ ተጉዛ ገብታ፡፡ ይችን ጥጥ ልብ ይዛቹህ አትፎክሩብን፡፡ ድንቄም! “አቅም ስለሌለን ልብ ስለሌለን ነው” ካላቹህ ደግሞ ዜጎች በሰላማዊ ትግል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉበትን መድረክ ክፍት ማድረግ ዕድል መስጠት ነዋ! ሁለቱንም ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ መፈናፈኛ አሳጥቶ ይሆናል እንዴ? ቦቅቧቃ ቅዘናም ሁሉ! እናንተ በተንቦቃቦቃቹህ በቀዘናቹህ ቁጥር እኛ ሰላም ማጣት መታመስ አለብን እንዴ?
እናንተን መንግሥት ብሎ ለማለት ባይቻልም አንድ መንግሥት ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው እንጅ ሕዝብ አይደለም ተጠሪነቱ ለመንግሥት
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
የሆነው፡፡ እናም ማንም የመሰለውን የቃዠውን ሁሉ አስገድዶ በሕዝብ ላይ መጫን አይችልም፡፡ ያለመቀበል ሙሉ መብት አለው፡፡ በምንም ነገር ላይ የመጨረሻው ባለሥልጣን ሕዝብ ነው፡፡ የሕዝብና የመንግሥት ሐሳብ ከተስማማና አንድ ልብ ከሆነ ብቻ መንግሥት የመሰለውን የማድረግ መብት አለው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይሄንን የመንግሥትና የሕዝብ ስምምነት ልናይ አልቻልንም እየተጠበቀና እየተፈጸመም ያለው የቡድን ጥቅምና ሐሳብ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዳጅና ጠላቱን አሳምሮ ያውቃል ነጋሪ አይፈልግም፡፡ የአንዳርጋቸውና የጓዶቹ ሐሳብ  ይጠቅመኛል ካለ ያንን የመቀበል ካላለ ደግሞ የመጣል ያለመቀበል ሙሉ መብት አለው፡፡ እናንተ ለራሳቹህ አንቀበልም አይስማማንም የማለት መብት አላቹህ፡፡ እናንተ እንዳላቹህ ሁሉም ሕዝቡም ደግሞ አለው፡፡ ይሄንን መብቱን በመንፈግ የእናንተን አስተሳሰብ በግድ በሕዝብ ላይ መጫን አይቻልም ወንጀል ነው ሕግ ይከለክላል፡፡ ይህ አንባገነንነት ፈላጭ ቆራጭነት ነው፡፡ ልታውቁት ልትረዱት ሊገባቹህ ያልቻለው ነገር ይሄ ነው፡፡ ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ ከእናንተና ከመሰሎቻቹህ በላይ ጠላት የለባቸውም፡፡ ደኅና ሁኑ
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

No comments:

Post a Comment